ትዝታ ነሽ ለ'ኔ
ጎሃ ካናቱ ላይ - ከኮረብታው ቆሜ ቁልቁል ስማትርሽ
የቆንጆ ልጅና - ያ'በባ መዓዛ ሲፈልቅ በጎዳናሽ
ካ'ዘዞ ቸቸላ - ከፒያሳ እንብርትሽ...እስከ አሸዋሜዳ
...ከብልኮ ጥጉ - ወዲህ እስከ አራዳ
አየሁ አንች ምድር!...
ውበትና ታሪክ - ከምድርሽ ሲመነጭ አንድነት ሲቀዳ፡፡
ምስጢር ነው ውበትሽ - ሲርቁት ይጠብቃል
ባ'መድ ማህፀን ውስጥ - ራሱን ሸሽጎ - እንደሚግም እሳት
ከውስጤ ተቀብሮ - ፈጀኝ ረመጡ - ጠበሰኝ መለየት፡፡
እርግጥ ደሮ ማታ - ላንድ ቀን ስንብት..ፍርሃትን ብኖርም
ደርዘን ወራት ሙሉ - መራገድን አርግዤ..ሀሳብን ባምጥም
ጣር ጥፍሮቹን ስሎ - መውጊያ ጦሩን ይዞ..በግንባሬ ቢቆም
መለየት አድብቶ - ጥላዮን ተጋርቶ..ስር ስሬን ቢከርምም
ዛሬ ከኔ ሸሽታ!!
መጥለም - መጥለቋን ግን.. እንዲህ አልጠበኩም፡፡
የምንትዋብ ማተብ - የታሪክ እመቤት..የቴዎድሮስ ፍቅሩ
ጎንደር አባ ጃሌ - የዞብል መስገሪያ.. የፋሲል መንበሩ
የሰቀዘኝ ውጋት - የመለየት ጦሩ..ቀለል እንኳን ቢለኝ
ስስት አትሁኝብኝ - እንደምንም ብለሽ..አስኮርፈሽ ላኪኝ፡፡
የሀይማኖት ደብር
የሊቃውንት አገር
የነገስታት ምድር
የታሪክ መዘክር
ትዝታ ነሽ ለ'ኔ
ትዝታ ነሽ ጎንደር፡፡
(ከረዘመ ትንፋሽ መድብል)
አስተያየቶች